የሀሳብ_ልዕልና_ለሁለንተናዊ_ብልጽግና !!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች በርካታ አዎንታዊ ለውጦችን አስመዝግባለች። እነዚህን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች አስጠብቆ ለማስፋት፣ ስህተቶችን ለማረም እንዲሁም የዛሬውንና የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ወቅቱ ለሚጠይቀው ትግል በሚመጥን መልኩ ለመደራጀት አምነው የፈፀሙትን ውህደት መነሻ በማድረግ ይህ የ”ብልጽግና ፓርቲ” ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።
ወጥ ዓላማ ያለው ኅብረ ብሔራዊ ውሑድ ፓርቲ መሆን ሰፊውን የሀገራችንን የሕዝብ ክፍል የሚያቅፉ ነገር ግን በዕይታ ግድፈት ከሀገራዊ የፖለቲካ ውሳኔ የተገለሉትን ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የሚሳተፉበትን ፓርቲያዊ አወቃቀር ለማምጣት ያስችላል። በሌላ በኩል ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲው አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮች በሚያሳትፍ እና በሚያካትት መልኩ ውክልና እና ብቃትን መሠረት ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ትሥሥሮሽን በማጠናከር በሐሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የፖለቲካ ፉክክርና ትብብር መሠረት እንዲይዝ በማድረግ ሀገራችን የተያያዘችው ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ሂደት ቀጣይነት ኖሮት ከማይቀለበስበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ እና እንዲጠናከር የሚያግዝ ይሆናል።በአጠቃላይ እውነተኛ ኀብረ ብሔራዊ የሆነው ውሑድ ፓርቲያችን የዓላማና የተግባር ውህደት በማምጣትና የተሻለ ኃይል በማሰባሰብ በቀጣይ ለላቀ የዓላማ አንድነትና ሀገራዊ ድል የሚያበቃ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ አቅጣጫ የሚከተል ይሆናል።
መለያ ዕሴቶቻችን
ኅብረ ብሔራዊ አንድነት
የዜጎች ክብር
ነጻነት
ፓርቲያችን ሀገራችንን የሚመለከትበት የዕይታ ማዕቀፍ በጥቅሉ የነበረውን ጠንካራ መሰረት በማስጠበቅ እና ውስንነቶችን በማረም ሁለንተናዊ የብልጽግና ምዕራፍ መክፈት የሚል ነው። ይህን የዕይታ ማዕቀፍ በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በተለያዩ ቡድኖች፣ መደቦች፣ ማንነቶች፣ ወዘተ የሚስተዋሉ ዋልታ- ረገጥ አስተሳሰቦች ሚዛን ጠብቀው እንዲሄዱ ያደርጋል።
የብልጽግና ፓርቲ ጥቅል ዓላማ፦ “የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ” የፓርቲያችን ጥቅል ዓላማ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው። ብልጽግና ስንል ፈርጀ ብዙ ትርጓሜን አዝሎ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና የማኅበራዊ ገፅታ ያለው ነው። የኢኮኖሚ ብልጽግና፣ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶች በተገቢና በዘላቂነት ለማሟላት ፈጣን እና ሁለንተናዊ ዕድገትን በማስመዝገብና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የህዝቦችን ድኅነትና ኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ መቻልን ያካተተ ነው። የፖለቲካ ብልጽግና ስንል ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመገንባት፣ የሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው የሚኖሩባት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ማለታችን ነው። የማኅበራዊ ብልጽግና መልካም ሀገራዊ ወጎችን፣ ዕሴቶችን እና ባህሎችን በማዳበር በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ማፍራት፣ በአካልና በአእምሮው የዳበረ ጤናማ ዜጋ መፍጠር፣ ከአስከፊ የማኅበራዊ ችግር የተጠበቀ ኅብረተሰብ መገንባት እና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ማለት ነው።
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው፣ የብሔር ማንነትን እና የሀገራዊ አንድነትን ሚዛን የጠበቀ ሀገረ-መንግስት መገንባት ነው። ከጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ አንፃር ፓርቲያችን ህዝብ ከቀጥተኛ የህልውና አደጋ ተጠብቆ የልማት፣ የእኩልነት እና የነፃነት ፍላጎቶቹ እንዲሟላለት የሚያስችል ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃትን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ ተቋማዊ አደረጃጀት መገንባት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል።
የፖለቲካ ፕሮግራም ግቦች
ጠንካራና ቅቡል ሀገረ መንግሥት በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሀገራዊ መግባባት መፍጠር
በተቋማዊና ሕዝባዊ ባህል ላይ የቆመ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት
ዘላቂና አዎንታዊ ሰላምን ማረጋገጥ
የኢኮኖሚ ፕሮግራም ዓላማ፡- ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት
የብልጽግና ፓርቲ በኢኮኖሚ ፕሮግራሙ የሕዝባችን ሰፊ ክፍል የሆነውን አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ወጣት፣ ሴቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች ማዕከል ያደረገ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የሕዝባችንን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ዓላማ ይኖረዋል። ፓርቲያችን በሀገራችን ምርታማነትን እና ፍትሐገዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ወሳኝ አቅምና መሣሪያ ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም የመንግሥት በኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ ያለው ተሳትፎ የገበያ መርሕን በመከተል ስትራቴጂካዊ በሆነ ሁኔታ ሀብት የሚፈጥር፣ በተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ማሕቀፍ ውስጥ የግሉን ዘርፍና ሌሎች የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ተሳትፎ በማጎልበት ምርታማነትን በላቀ ደረጃና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያሳድግ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህም መሠረት ፓርቲያችን ጥራት ያለውና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ሀገራችንን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሸጋገር ያልማል።
የኢኮኖሚ ፕሮግራም ግቦች
የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባት
ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ልማት እና ምርታማነትን መሰረት ያደረገ ማኅበራዊ ፍትሕ ማረጋገጥ
ሀብት ፈጠራን የሚያሳድግ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ መገንባት
ከተሜነት እና የከተማ ልማትን ማስፋፋት
የየማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማ፡- ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ አካታች ማኅበራዊ ልማት
ሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መነሻዋ ዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ሁለንተናዊ ማኅበራዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዳይ የፓርቲያችን የማኅበራዊ ፕሮግራም አንድ ዋና ትኩረት ይሆናል። በመሆኑም የማኅበራዊ ልማት ሥራዎቻችን የዕድገትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መንትያ ግቦችን የማሳካት ጉዳይ ይሆናል። ማኅበራዊ የልማት ሥራዎቻችን ከችሮታና ከነባሩ የማኅበራዊ ደኅንነት ትኩረት ወጥቶ ችግሩን ከመብት አንፃር የሚመለከተው ይሆናል። የማኅበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተደራሽነትና አካታችነት ባለው መልኩ የማኅበረሰብን ጤና፣ ደኅንነት እና ምቾት የሚያስጠብቅ መሆን ይኖርበታል። ማኅበራዊ ፕሮግራማችን ዜጎችን የሚያስተሣሥር፣ ከችግርና ከመከራ የሚታደጋቸው፣ የሀገርን አለኝታነት የሚያሠርጽ እና በሀገራችን አዎንታዊ ሰላምን የሚያረጋግጥ ይሆናል። ማኅበራዊ የልማት ፕሮግራማችን ኅብረ ብሔራዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብት እንዲሆን ዒላማ አድርጎ መንቀሳቀስ የፓርቲያችን የማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማ መገለጫ ይሆናል። ይህንንም እውን ለማድረግ በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን፣ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማ ነዋሪ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የዜጎች አገራዊ አገልግሎት እንዲስፋፋ ፓርቲያችን ይሰራል።
የማኅበራዊ ፕሮግራም ግቦች
ፍትሐዊነት፣ ጥራት እና አግባብነት ያለው የትምህርትና ስልጠና ስርዓት ማረጋገጥ
መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ሥርዓት መዘርጋት
የሀገራችንን ዐቅም ያገናዘበ የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት
የሴቶችንና ወጣቶች የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጎልበት
ብዝኃነታችንን ማዕከል ያደረግ የቋንቋ የባህልና ቅርስ ልማት
የውጭ ግንኙነት ዋና ዓላማ፡- ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት
ፓርቲያችን የውጭ ጉዳይን ከሀገር ውስጥ ጉዳይ የተነጠለ አድርጎ አይመለከትም። ይልቁንም የሀገር ውስጥ ጉዳያችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ለውጦች ነፀብራቅ ሆኖ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያልዘነጋ ነው። የውጭ ግንኙነታችንም የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታን የሚያረጋግጥ፤ የሀገር አንድነትን በማስጠበቅ ሀገራዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ፤ ሀገራዊ ክብርን በማጎናጸፍ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ይሆናል። ሀገራዊ ክብር የሌለው ሀገር ሀገራዊ ጥቅሙን ሊያስጠብቅ እንደማይችል ፓርቲያችን በጥብቅ ይገነዘባል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ታሪክ እና አንድነት እንዲሁም የዜጎቿን ክብርና ተስፋዋን የሚያንፀባርቅ የጋራ ስምምነት ያለው ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ የተቀናጀና የተማከለ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ትግበራን እውን ያደርጋል። ሀገራዊ ክብራችንን ለማረጋገጥ እና ጥቅሞቻችንን ለማስከበር፣ አስቀድሞ ግንኙነትን በማደስና በማጠናከር ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መሥራት ላይ ትኩረት በማድረግ በግንኙነት ብልሽት ምክንያት የምናጣቸውን ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር አመች ሁኔታ ይፈጥራል። በውጭ ግንኙነት መስክ ሀገራችን መልካም የሚባል ውጤት ያስመዘገበች ሀገር ብትሆንም የውጭ ግንኙነታችን ከጉድለት እና ከግድፈት የጸዳ አይደለም። ስለዚህ ግድፍቶቹን እና ጉድለቶችን መለየት፣ ማስተካከል እና መሙላት እንዲሁም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠል የፓርቲያችን የውጭ ግንኙነት መሠረቶች ናቸው።
የውጭ ግንኙነት ግቦች
ሀገራዊ ክብርን የሚያረጋግጥ የውጭ ግንኙነት
ለትብብርና ለጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አጋሮቻችንን ማስፋት
የብዙዮሽ ትብብር ተቋማት ተሰሚነትን መጨመር እና ፖሊሲያዊ ነጻነትን ማስከበር
ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ
የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ማሳደግ
ሀገራዊ ክብርን እና ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የውጭ ግንኙነት የመፈፀም አቅም መገንባት